top of page
Search

#የአፋብን_መንገድ_ወደዬት_እያመራ_ነው???

eyobabyssinia
Aug 31
5 min read

ለአፋብን ከአማራ ሕዝብ እና ከጽምዶ ማን ያዋጣዋል??

አፋብን ከአማራ ሕዝብ እና ከጽምዶ መካከል አንዱን ለመምረጥ የተገደደበት ደረጃ ላይ ሆናል-!!



***ወንድወሰን ተክሉ***


የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ባሰማራቸው ደርዘን ያህል ልሳኖቹ ተጠቅሞ የጽምዶን ፍጹማዊ አዳኝነትን መስበክ ከጀመረ ሰነባብታል። ጽምዶ ማለት ስርወ ቃሉ እራሱ ትግሪኛ ሲሆን ትርጉሙም መጣመድ ማለት ነው። ሁለት የተጣመዱ በሬዎች ጽምዶ ይባላሉ። የቃሉ ባለቤት ትግሪኛ ተናጋሪ ወገኖች እንደሆኑ ሁሉ የጽምዶን ህልውና ያበሰሩት ሁለቱ ተጎራባቾች ህወሃትና ሻእቢያ ቢሆኑም ዋናው አጣማጅ ግን የሻእቢያ መንግስት ነው። ሻእቢያና ህወሃት መጀመሪያ ከተጣመዱ በኃላ የጥማድ አድማሳቸውን በማስፋት የሱዳኑን አልቡርሃን መንግስት፣ የአማራውን አፋብን፣ የኦሮሞውን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት (OLA) የአፋሩን አፋጉጉ እና የቤኒሻንጉል ጉምዙን የጉሙዝ ታጣቂን ያካተተ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥማድ እንደፈጠሩ የአፋብን አመራሮችና የህወሃት ልሳኖች እየገለጹ ነው።


በተለይም የአፋብን ልሳኖች የሆኑት ግሳንግስ ብሎገሮች 7/24 ሰዓት ጽምዶ ያድናል፣ ጽምዶን ያልተቀበለ ይጠረጋል፣ ጽምዶን ያልተቀበለ የኦህዴድ መራሹ የብልጽግና መንግስት ስልጣን አስቀጣይ ነው እያሉ መሀይማዊ የፍረጃ ልሳናቸውን ማጮህ ከጀመሩ እጅግ ቢሰነባብቱም አንዳቸውም ግን የጽምዶን ለአማራ ሕዝብ የሚያመጣውን ጥቅም እና የአማራን ሕዝብ የሚያስከፍለውን ዋጋ ፈጽሞ ገልጸው አያውቁም።


እንዱሁ በደፈና፣ ሾላ በድፍኑ ጽምዶ ያድናል ተቀበሉ ነው እያሉን ያሉት። የእነዚህን በቀቀኖችን መሀይማዊ ጩህት ወደ ጎን አድርገን እስቲ ስለጽምዶና የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል እንመልከት ።


ሰባት አባላትን ያቀፈው የጽምዶ ሥብስብና አማራ ምን እና ምን ናቸው ብለን መፈተሽ ስንፈልግ - የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው ሲፈጁና ሲያስፈጁ የቆዩ ህወሃትና ኦነግ OLA እና የጉምዝ ታጣቂ ያሉበት ሲሆን በተለይም ከሁለቱም ጋር የግዛት ይገባኛል ጥያቄ - ማለትም ከህወሃት ጋር የወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራ፣ ራያና አላማጣ በህወሃት በኩል የይገባኛል ጥያቄ አንስታ በወረራ የተያዙ ግዛቶቼ ናቸው ባይ ነች። በ OLA በኩል በአዲስ አበባ ላይ የማንደራደራ የኦሮሞ ንብረትና ዋና ከተማ ነች በማለት መላው የአማራ ሕዝብ ከሚያምንበት ከተማይቱ የመላው ኢትዮጲያዊያን ንብረት የሆነች የኢትዮጲያና የአፍሪካ ሕብረት ዋና ከተማ ናት ከሚለው አቃም ጋር እጅግ የተቃረነ አቃም ያለው ድርጅት ነው።


በተጨማሪም ሁለቱም ድርጅቶች ማለትም ህወሃትና OLA በሀገረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ የዛሬውና ነገደ አማራን ህልውናን አደጋ ላይ የጣለውን ሕገ መንግስት ጫፉን መነካት የሌለበት ምርጥ ሕገ መንግስት ነው በማለት የአማራ ሕዝብ ህልውናውን ለማስጠበቅ ከሚታገልለት ዋና አላማ ጋር በተቃርኖ የቆሙ ናቸው። የጉምዝ ታጣቂም ከሆነ ከአራትና አምስት አመት በፊት ወገኖቻችንን በመተከል ምድር በግሬደር ያስቀበረን ጸረ አማራ ጨፍጫፊያችን ሲሆን በአፋር በኩል ብቻ ነው ምንም ችግር እንደሌለን የምናየው።


ወደ ሁለቱ የጽምዶ አባል የውጭ ሀገራት ኤርትራና ሱዳን ብንመጣ ከሱዳን ጋር እንደ አማራነታችን በተለየ ሁኔታ የምንወዛገብበት ነገር ቢኖር በአቢይ አህመድ ከአምስት አመት በፊት ተላልፎ የተሰጠውን የአልፋሺጋን መሬት በስተቀር የመወዛገቢያ የግዛት ይገባኛል ጉዳይ የሌለን ሲሆን በኤርትራ በኩል በሁለታችንም ዘንድ የግዛት ይገባኛል ውዝግብ የሌለን ጥሩ ተጎራባቾች ብንሆንም ሁለቱ የጎረቤት ሀገራት ኤርትርኝ ሱዳን የጽምዶ አባል የተደረጉት ከቁጥር ማብዛት ድምቀት የዘለለ በኢትዮጲያ ውስጥ ሰራዊታቸውን ልከው ከአቢይ ጋር የሚዋጉበት ምክንያት ፈጽሞ ስለሌላቸውና ለእኛም ብለው ሰራዊት ልከው ሊዋጉልን እንደማይችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት የአትኩሮት አቅጣጫችንን በአማራ እና በህወሃት፣ በአማራ እና በOLA መካከል ሊካሄድ ስለሚቻለው ጸረ ብልጽግና ግንባር በሉት ጥምረት (ጥማድ) ጉዳይ እንመለከታለን።


በፖለቲካው አለም ማንኛውም አይነት ድርጅት ከፈለገ ከየትኛውም አይነት ድርጅት ጋር ጥምረትም ሆነ ትብብር፣ አሊያም ግንባር ሲፈጥር ማየት ምንም አዲስ አይደለም። የሚፈጠሩት ጥምረቶች በሙሉ ግን በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርቶ የሚከናወን መሆኑ ላይ ተግባብተን ጉዳያችንን ወደ ማየቱ እናምራ።


የአማራ ፋኖ እና የትግራዩ ህወሃት ጸረ አቢይ ግንባር ለመፍጠር በምን ተስማሙ?? ማን ምን ሰጥቶ ከሌላኛው የአጸፌታ ስጦታ በመቀበል ነው በጋራ አንድ ጥምረት መፍጠር የሚችሉት? ወይም እንደነ ዘመነ ካሴ አገላለጽ Already ጥምረቱን መፍጠር የቻሉት ??


አቢይን በጋራ ለመታገል መፈለጋቸው ብቻ እነዚህን ሁለት የተለያየ ጠርዝ የረገጡ ኃይሎችን በአንድ ጥላ ስር ማሰባሰብ ይቻላልን?? እሺ የማይቻለው ተቻለና በአላማና በግብ ፈጽሞ የማይስማሙና የማይመሳሰሉ እነዚህ ኃይሎች Just for the sake of removing abiy from office ተባብረው ጥምረት ሆነ ግንባር ቢመሰርቱ እና ድል ቢቀናቸው የሚያመጡት ውጤት ምን ይሆናል ብለን እስቲ እራሳችንን እየጠየቅን ለመልሶቹም ምላሽ እንእንፈልግላቸው።



እነዚህ ሰባት ሀይሎች ጥምረት ሲፈጥሩ ዝም ብለው አቢይ አህመድን ብቻ ለማስወገድ አይደለም የተጣመሩት/ የሚጣመሩት። አቢይን ለማስወገድ የፈለጉበትን ምክንያት ከአቢይ መወገድ በኃላ ተመልሶላቸው ማየት ስለፈለጉ ነው ጥምረቱን የፈጠሩት። የሱዳንና የኤርትራ በዚህ ጥምረት ውስጥ መካተት አቢይ መራሹ የብልጽግናው አገዛዝ በሁለቱ መንግስታት ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብ እጆቹን ስለዶለ ያንን እጅ ቆርጠው በማስቀረት ቀጣዪ መንፍስት ተመሳሳይ የጣልቃ ገብነትን ፖሊሲ እንዳያራምድ ከመሻት አንጻር ከኢትዮጲያዊያኑ አማጺዎች ጋር ለመጣመር ችለዋል።


የአማራው ፋኖ፣ ( አፋብን) የትግራዪ ህወሃት እና የኦሮሞው OLA ተመሳሳይ አንድ ብልጽግና የሚባል ጠላት በጋራ ግ። በየፊናቸው የሚታገሉ ቢሆንም ሶስቱም ብልጽግናን የሚታገሉበት ምክንያትና ከብልጽግና መፍረስ በኃላ ሶስቱም መፈጸም የሚፈልጉት አላማ ፈጽሞ የተለያየ ነው።


1ኛ- የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ።

የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል የተወለደው ህልውናውን አድርጋ ላይ በመውደቁ ሲሆን የዚህ የህልውና ትግል የመጨረሻም ግብ የህልውናውን አደጋ የሆነውን ህወሃት መራሹ ኢሕአዴግ በ 1987 ያጸደቀውን ሕገ መንግስት መቀየር ወይም በማሻሻል አዲስ ሕገ መንግስት አርቅቆ ( ከሌሞች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር) ህልውናውን ማረጋገጥ ነው። ይህንን ሲያደርግ የኢትዮጲያን ሉአላዊ ግዛትና አንድነት በጠበቀ መልኩ ሲሆን በማንነቱ እየለዪ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የፈጸሙበትን ግለሰቦች፣ቡድኖችና ምናባትም ድርጅቶችን ወደ ፍትህ ደጃፍ በመውሰድ ፍትህን ለመጎናጸፍ ነው። ይህን። ለማድረግ ከዚህ አላማ ጋር ከሚስማማ ማንኛውም ኃይል ጋር የመተባበር ችግር የሌለበት ሲሆን አቢይን ለመጣል በሚደረግ ትግል ሂደት አጋዥ ኃይል አመጣለሁ በሚል እምነት መክፈልና መስጠት የማይፈልገውን በመስጠት አጋርነትን አመጣለሁ ብሎ አያምንም። ለአብነት ህወሃት ከአማራ ጋር እንድትሰለፍ የወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራና ራያን ግዛቶቹን ለህወሃት መስጠትና መልቀቅ አለብኝ ብሎ ቅንጣት ታህል አያምንም።



2ኛ- የህወሃት ከብልጽግና ጋር የምታደርገው ግብግብ እንደ አማራው ለስርነቀል ለውጥ ሳይሆን በወረራ የተያዙብኝ የምትላቸውን የአማራን ግዛቶች መልሳ በእጃ ለማድረግ፣ የተነጠቀቺውን የፓርቲነት ፍቃድ መልሳ ለማግኘት፣ የታገዱ የኢኮኖሚ ጥቅማጥቅሞች እንደሚለሱላት ለማድረግና የተፈናቀሉ ትግራዋዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ሲሆን ከተቻላት ደግሞ Ultimately የትግራይን ክልል ገንጥሎ ሀገር ለማድረግ ነው ።


3ኛ- የኦሮሞው OLA የሚታገለው አዲስ አበባን የኦሮሚያ ዋና ከተማ ያደረገች የኦሮሚያን ሪፐብሊክ ለመመስረት ከብልጽግና ጋር የሚታገል መሆኑን ስንመለከት እነዚህ ሶስት ዋና የጽምዶ ተዋናይ ኢትዮጲያዊያን ኃይሎች ጋር አንዳችም የጋራ አንድነት ፈልገን ስናጣ እናያለን።


የአላማ አንድነት የሌላቸው ሶስት ወሳኝ ኢትዮጲያዊያን የታጠቁ ኃይሎች አንዳችም የጋራ አላማና ግብ ሳይኖራቸው እንዴት እድንድ ጥምረት ሊፈጥሩ ቻሉ ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ በአማራ ሕዝብ ዋጋ ከፋይነት ይህ ጸረ አቢይ የተባለው ጥመረት/ጽምዶ ሊፈጥሩ እንደቻሉ ነው መረዳት የሚቻለው። ከላይ በመግቢያዬ የጽምዶ ባለቤትና ፈጣሪ ህወሃትና ሻእቢያ ናቸው ስላችሁ የአማራ ፋኖ - ማለትም የአፋብን አመራሮች በዚህ ጥማድ ውስጥ ገብተው ተሳታፊና እነሱ እንደሚሉት ተጠቃሚ ለመሆን:-


1ኛ- የአማራን ግዛቶች ወልቃይት ፣ ጠገዴ፣ ሁመራ፣ ራያና አላማጣ የአማራ ሳይሆኑ የወያኔ ናቸው ብለው በመፈረም ነው። ለምሳሌ የወሎ ቤተአምሃራዎቹ እነ ሄኖክ ኪዳኔ በእኛ በኩል የአማራ ቀይ መስመሮች የምንላቸው የሉም። ራያና አላማጣን ሰጥተናል፣ እናንተም እንደ እኛ ስጡ በማለት ለጎንደር በላይ እዝ አመራር አባላት አዘዋቸዋል።


2ኛ- የስርነቀል ለውጥ አላማ ተሰርዞ በምትኩ አቢይን በመተካትና አሁን የአገዛዙ መተዳደሪያ የሆነው ሕገ መንግስት እንዲቀጥል ተስማምተን ነው ማለት ነው።


3ኛ- አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማም ናትና ህገ መንግስቱንም መነካት የለበትም የሚለውን የ OLA አቃም የእኛ ሰዎች- የአፋብን አመራሮች በመቀበላቸው ነው ከጽምዶ ጋር መጻመድ እንደቻሉ የምንረዳው።



ታዲያ ይህ ጥምረት ለአማራ ሕዝብ የሚያመጣው ትርፍ ምንድነው ?? ብላችሁ ለምትጠይቁ በአማራ ፋኖ ስም ይህንን የጽምዶን ጥምረት ውስጥ ለመግባት አማራን ወክሎ የተደራደረው አካል ወፈር ያለ የስልጣን ባለቤት ይሆናም። ከቀናው አዲስ አበባ ላይ፣ ካልሆነም በባህር ዳር ላይ ይህንን ስምምነት ያደረገው አመራርና ባልደረቦቹ የስልጣን ጥቅም ተቃዳሽ ከመሆን የዘለለ የአማራው በማነቱ እየተለየ የመገደሉ ሁኔታ እንዱቀጥል የሚያደርገው ሕገ መንፍስት ንክች አይደረግም። የአማራ ግዛቶች የሆኑት እንደነ ወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራና ራያ ለህወሃት ይመለሳል። አዲስ አበባም የኦሮሞ ሆና በኦሮሚያና መሰል ክልሎች የሚኖረው አማራ መጤ እየተባለ መገደሉ፣ መፈናቀሉና መባረሩ ይቀጥላል።


መለስ ዜናዊ በ 2012 ሲሞት የአማራ ግድያ ይቆማል ብለው የገመቱ ብዙ የዋሆች ነበሩ። ሀይለማሪያም ተተክቶ ግድያው አልቆመም። አቢይ አህመድ ተተክቶም ግድያው እጅግ ባሰ እንጂ ፈጽሞ አልቆመም ። ምክንያቱም የግድያዎቹ ምንጭ ሕገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው ሕግ እንጂ ግለሰቦቹ ብቻ አይደሉም።


በዚህ ሂደት ውስጥ ጥቂት የአፋብን አመራሮች ከሰፊው የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ጥያቄና ግብ ይልቅ በህልውናው ትግል ስም የግላቸውን ፍላጎት ለማርካት ህወሃትንና ጽምዶን መምረጣቸውን Favor እንዳደረጉ ግልጽ ነው። ይህ ምርጫቸው ግን እነሱ እንዳሰቡት ለስልጣን የሙበቁበት ምርጫ ሳይሆን ከአማራ ሕዝብ ተተፍተው የፖለቲካን ሞት የሚሞቱበት ምርጫ መሆኑን ፈጽሞ አልተረዱም። ከአማራ ሕዝብ እና ከጽምዶ መካከል አማርጦ ጽምዶን የመረጠ የፋኖ አመራር ግለስብ ሆነ ቡድን፣ ወይም ድርጅት ከባህር የወጣ አሳ ይሆናል።



ለመሆኑ ከባሕር የወጣ አሳ ህይወት ይኖረዋልን??

በ1985/6 ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ወጥቶ ጫካ ከገባ በኃላና ከገባበት ጫካ በህወሃት ተቀጥቅጦ ተሸንፎ የተያዘው ተይዞ አመራሮቹ በቦሌ ወደ ኬኒያ ናይሮቢ እንዲፈረጥጡ ከተደረገ በኃላ መለስ ዜናዊ ኦነግ ከባሕር ውስጥ የወጣ አሳ ሆናል ብሎ ተናግሮ ነበር። ከሚታገልለት ሕዝብ መሀል የወጣ ማንኛውም ድርጅት ከባህር የወጣ አሳ ይሆናል።


አንድ በትጥቅ ትግል የሚታገል ድርጅት ይቅርና በስላማዊ ትግል የሚታገል ድርጅት እንካን ቢሆን የተነሳበትን የሕዝብ ጥያቄን ለግል ቅንጥብጣቢ ጥቅም ብሎ የህዝቡን የትግል አላማ በጣለበትና በሸጠበት ቅጽፈት በሕዝብ ውስጥ እያለ እንካን ሕዝብ አንቅሮ ይተፋውና ከባሕር የወጣ አሳ ሆኖ የፖለቲካን ሞት ይሞታታል። ብዙ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል።


የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ጥቂት አመራሮች በጽምዶ ጉዳይ ከተወለዱበት የአማራ ሕዝብ ጥያቄና አላማ ይልቅ የጽምዶ መስራችና ባለቤት የሆነቺውን ህወሃት የመረጡ መስለዋል። ውሳኔያቸውን በፍጥነት ካላስተካከሉ ከባህር የወጣ አሳ ሆነው የፖለቲካን ሞት ይሞታሉ። እናም የአፋብን አመራር ዳግም ከአማራ ሕዝብ እና ከጽምዶ መካከል አንዱን መምረጥ አለባቸው። ሁለቱ ፈጽሞ የማይዋሀዱ ውሃና ዘይት ናቸው። አበቃሁ።

 
 
 

Recent Posts

See All
የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ እና የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል

የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ እና የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር በከፍተኛ ውስብስብነት፣ በመዋቅራዊ ውጥረት እና በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መጋጨት ውስጥ ይገኛል። በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጎልተው የሚታዩትን የሶስቱን ዋና ዋና ወገኖች አቋም፣ የትግል አቅጣጫ እና

 
 
 

Comments


bottom of page