top of page
Search

የ“60ዎቹ” ግድያ እና ታሪካዊው ደብዳቤ !

  • eyobabyssinia
  • Nov 23, 2025
  • 3 min read

የ“60ዎቹ” ግድያ እና ታሪካዊው ደብዳቤ !

—————

መስከረም 2/1967 የደርግ የመጀመሪያው አዋጅ “ያለ ምንም ደም” በሚል ማርሽ ታጅቦ ቢታወጅም በህዝቡ ውስጥ ፍርሃት የለቀቀው በዚያው ቅጽበት ነው፡፡ አዋጁ በአንድ በኩል ዘውዳዊ ስርወ-መንግሥት ማብቃቱን ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል የአዋጁ ስምንተኛ አንቀጽ “ይህ አዋጅ እስከጸናበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን ዓላማ በመቃወም አድማ ማድረግ፣ ስራ ማቆም፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማድረግ፣ በጠቅላላው የህዝብን ጸጥታ እና ሰላም የሚነሳ ተግባር መፈጸም ክልክል ነው” በማለት በህዝቡ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ እቀባ ጥሏል፡፡ ቢሆንም በመነሻው ላይ የህዝብ ድጋፍ ያገኘው ወታደራዊ መንግሥት የህዝቡ ተቃራኒ ሆኖ ወደ ጭፍጨፋ ያመራል የሚል ግምት አልነበረም፡፡

መስከረም ሲብት በአዋጁ የተነገረው ዛቻ ወደ ድርጊት ተሸጋገረ፡፡ ንጹሐን ያለ ፍርድ ተገደሉ፤ ተረሸኑ፡፡ በጥቅምት ወርም ግድያና አፈናው ቀጠለ፡፡ ህዳር 13/1967 ላይ ከጡዘቱ ጫፍ ላይ ወጣ፡፡ የመጀመሪያው የደርግ ሊቀመንበር የነበሩትን ሌተና ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶምን ጨምሮ የአጼ ኃይለሥላሤ መንግሥት ሚኒስትሮች፣ የክፍለ ሀገር ገዥዎች፣ እንደራሴዎች፣ የጦር መሪዎችና ሌሎች ባለስልጣኖች የሚገኙባቸው 60 ሰዎች በአንድ ምሽት ያለ ፍርድ ተረሸኑ፡፡


*


ደርጎች ለስልሳዎቹ ግድያ ንዑስ ደርግ የሚባሉትን ትንንሽ ኮሚቴዎች ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ ሲያሰኛቸውም “ጄኔራል አማን ሚካኤል ስላስከፉን በግብታዊነት ተነስተን ለሳቸው የሰነዘርነው በትር ሌሎችንም ሰለባ አደረጋቸው” ይላሉ፡፡ ይሁንና እውነታው ሲገለጽ ስልሳዎቹ ሰዎች በሁሉም የደርግ አባላት ስምምነት መሰረት መሆኑ ታውቋል፡፡ በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት ሁሉም የደርግ አባል የግድያው ተሳታፊ ነበር (ደብዳቤውን አሳድጋችሁ እዩት፡፡ ወይንም ዳውንሎድ አድርጉት፡፡ በያኔው ሻለቃ መንግሥቱ ሀይለማሪያም የተፈረመ ነው)፡፡


ደብዳቤው ሀምሳ አራት ባለስልጣናት ነው የሚለው፡፡ የተገደሉት ግን 60 ሰዎች መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል በተራ ቁጥር 59 እና 60 ላይ የተጠቀሱት ወታደሩ ራሱ የመረጣቸው የደርግ አባላት ናቸው እንጂ የሀይሌ ስልሳ መንግሥት ባለስልጣናት አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ (እንደ ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ ያሉት) በደርግ ላይ ሸፍተዋል ተብለው የተያዙ ናቸው፡፡ እንደ ልዑል እስክንድር ደስታ ያሉት ደግሞ በንጉሣዊ ቤተሰብ አባልነታቸው ብቻ ነው የተገደሉት፡፡


እነዚህ ሰዎች በኃይለሥላሤ መንግሥት ዘመን በነበራቸው ስልጣን ተጠቅመው ህዝቡን በድለውት ከሆነ መቀጣታቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ቅጣቱ የተፈጸመው በፍትሐዊ መንገድ አይደለም፡፡ በአንድ ሌሊት በጅምላ ተረሽነው በአንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ ነው የተደረገው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የጅምላ ግድያ ምንጊዜም ቢሆን ሊወገዝ የሚገባው ነው፡፡


*


60ዎቹ ሰዎች የተገደሉት ህዳር 13/1967 ሌሊት ከምሽቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ውጤቱ ለህዝቡ የተገለጸው ደግሞ በማግሥቱ ህዳር 14/1967 ነው፡፡ በዚያች ምሽት የተገደሉት ስልሳ ሰዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡


1. ሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም

2. ጸሓፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ

3. ራስ አስራተ ካሳ

4. ልጅ እንዳልካቸው መኮንን

5. ራስ መስፍን ስለሺ

6. ሌ/ኮ/ ታምራት ይገዙ

7. አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ

8. ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚእ

9. አቶ ሙላቱ ደበበ

10. አቶ አበበ ረታ

11. ደጃች ሰለሞን አብርሃም

12. ደጃች ለገሰ በዙ

13. ደጃች ሳህሉ ድፋዬ

14. ደጃች ወርቅነህ ወልደ አማኑኤል

15. ደጃች ክፍሌ እርገቱ

16. ደጃች ወርቁ እንቁስላሤ

17. ደጃች አዕምሮስላሴ አበበ

18. ደጃች ከበደ ዓሊ ወሌ

19. ኮሎኔል ሰለሞን ከድር

20. አፈንጉሥ አበጀ ደባልቄ

21. አቶ ነቢየልዑል ክፍሌ

22. ቀኛዝማች ይልማ አቦዬ

23. አቶ ተገኝ የተሻወርቅ

24. አቶ ሰለሞን ገብረማሪያም

25. አቶ ሀይሉ ተክሉ

26. ልጅ ሀይሉ ደስታ

27. ብላታ አድማሱ ረታ

28. ፊታውራሪ ደምስ አላምረው

29. ፊታውራሪ አምዴ አበራ

30. ፊታውራሪ ታደሰ እንቁስላሴ

31. ሌ/ጄ/ አቢይ አበበ

32. ሌ/ጄ/ ከበደ ገብሬ

33. ሌ/ጄ/ ድረሴ ዱባለ

34. ሌ/ጄ/ አበበ ገመዳ

35. ሌ/ጄ/ ይልማ ሺበሺ

36. ሌ/ጄ/ ሀይሌ ባይከዳኝ

37. ሌ/ጄ/ አሰፋ በየነ

38. ሌ.ጄ/ በለጠ አበበ

39. ሌ/ጄ/ ኢሳያስ ገብረሥላሤ

40. ሌ/ጄ/ አሰፋ ደምሴ

41. ሌ/ጄ/ ደበበ ኃይለማሪያም

42. ሜጀር ጄ/ ስዩም ገድለ ጊዮርጊስ

43. ሜ/ጄ/ ጎሹ ከበደ

44. ሜ/ጄ/ ታፈሰ ለማ

45. ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ

46. ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ ወልደዮሐንስ

47. ብርጋዲየር ጄኔራል ወንድሙ አበበ

48. ብርጋዲየር ጄኔራል ግርማ ዮሐንስ

49. ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ

50. ኮሎኔል ጣሰው ሞጆ

51. ኮሎኔል ይገዙ የማነ

52. ሻለቃ ብርሃኑ ሜጫ

53. ሻምበል ሞላ ዋቅኬኔ

54. ሻምበል ደምሴ ሺፈራው

55. ሻምበል በላይ ጸጋዬ

56. ሻምበል ወልደ ዮሐንስ ዘርጋው

57. ም/አስር አለቃ ተክሌ ሀይሌ

58. ተራ ወታደር በቀለ ወልደ ጊዮርጊስ

59. መቶ አለቃ ተስፋዬ ተክሌ

60. ጁ/ኤክማን ዮሐንስ ፍትዊ


ምንጭ ኢትዮ ሰገነት ሚዲያ

 
 
 

Comments


bottom of page