ስለ አርበኛ #አስክንድር_ነጋ በጥቂቱ፡
- eyobabyssinia
- Jan 27
- 5 min read

ስለ አርበኛ #አስክንድር_ነጋ በጥቂቱ፡
በአማራ ፋኖ ትግል ብዙ የሚጯጯሁ ነገሮች ቢኖሩም በዚህ የጽናት ተምሳሌት በሆነው በታላቁ እስክንድር ነጋ ላይ ብዙ ሃሰቶች ሲናፈሱ በማየቴ በትግሉ አጋጣሚ በቅርበት የማውቀውን ለሃቅ ፈላጊ ህዝብ በጥቂቱ ለመጻፍ የእውነት አምላክ የቀሰቀሰኝ ይመስለኛል።
ታጋይነት ፣ጀግንነት፡ምሁርነት ሰዎች የሚፈሩትን እውነት በመድፈር የሃሰተኞችን ግፊያ መቋቋም መቻል ነው።
አርበኛ እስክንድር ነጋን ለዘመናት ከልጅነታችን ጀምረን በተለያዩ ሚዲያዎች በርቀት ከማውቀው በላይ በህይወት የትግል ጉዞ አጋጣሚ በአማራ ፋኖ ትግል ውስጥ ከሚደረገው ፈታኝ የትግል አጋጣሚ ደረጃየ ባይመጥነኝም ከተራ አባልነቴ አመራር ሆኜ ትግል እስከቀጠልኩበት አሁን ድረስ ከታላቁ እስክንድር ጋር የመሥራት አጋጣሚ ስለነበረኝ መሬት ላይ ተጨባጭ ማንነቱን ከማንኛውም መስካሪ የተሻለ እውነት እያለኝ ዝም ለማለት አልቻልኩም።
************
አርበኛ እስክንድር ነጋ በሕይወቱ ውስጥ ሃቀኝነትን መርህ ከማድረጉም በላይ የጽናት ተምሳሌት ነው። አማራ ታሪኩን ያድሳል በሚለው ቀደምት ንግግሩ በአማራ ፋኖ ነጻነት ትግል ላይ በገቢር መሬት ላይ የከፈለው ዋጋ ከጨቋኝ ሥርዓተ መንግስት ጋር በመታገሉ በእሥር ቤት ከ 11 ዓመት በላይ ስለ ህዝብ መከራን ከተቀበለበት በላይ በፋኖነት ዋጋን በመክፈል የታወቀ አርበኛ ነው።
አርበኛ እስክንድር ነጋ ከአማራ ትጉሃን ሊቃውንት ቤተሰብ ከመወለዱም በላይ ጣሊያንን ድል ካደረጉ አርበኞች መንፈስ የተወለደ እርሱም ለአርበኝነት ብዙ ጀግኖችን የወለደ መሆኑን ለመረዳት አርበኛ መከታው ማሞን እና ሌሎች አያሌ የአማራ ፋኖ ትግል መሥራቾችን ጠጋ ብሎ መረዳት ይጠይቃል።
አርበኛው ከቅንጡ የዚህ ዓለም ህይወቱ ዝቅ ብሎ ፔስታል አንግቶ ሸበጥ ተጫምቶ ሰውነቱ ከስቶ እና ገርጥቶ ሜዳና ተራራው ሳይበግረው ጎጃም እና ጎንደር ፣ወሎ እና ሸዋን ሲመላለስበት መቆየቱን ሰነፎች እንደ ደካማ ተግባር በመቁጠር ሲሳለቁ እንደማየት የሚገርም ነገር የለም። ሰዎች በዲቪ፣በጥገኝነት፣ በስደት እናት አገራቸውን ጥለው ለመመነን ስንት ዋጋ የሚከፍሉላትን ስንቶች ከመንግስተ ሰማያት አብልጠው የሚጓጉላትን አሜሪካ ከመ ጤፍ ሳይቆጥር እናት ሃገሬ ኢትዮጵያ ወገኔ አማራ ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ ደረሰበት ብሎ ከዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋችነት እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ሙያዎቹ ቅድሚያ ሰጥቶ በሚታገልለት ይህ የአማራ ፋኖ ትግል ውስጥ አብነት ሆኖ ይግኛል።
አርበኛ እስክንድር ነጋ ባለማወቅ እና በግለሰቡ ስኬታማ ጽናት እንድሁም ዓለም አቀፍ ዝናው የሚቀኑበት ስለርሱ የስም ማጠልሸት ዘመቻ ሳይታክቱ ቢለፉም እሱን ግን ከዓላማው ሸብረክ ሳይል አሁንም እንደቆመ ይገኛል።
ይህ አርበኛ በትግሉ ከከፈለው የትግል መከራ በላይ በጠላት የአቢይ መንግስት በተደጋጋሚ በድሮን ጥቃት ቢሞከርበትም ለብዙ ጊዜያት ከፍተኛ የድምሰሳ ኦፕሬሽን ሲሞከርበት እኔ ጸሐፊው አብሬ ነበርኩኝ።
አርበኛው ከሊቅነቱም በላይ በክፍለ ዘመኔ ድጋሚ ላገኘው የማልችለው ትሁት ከመሆኑ የተነሳ ታላቁም አትበሉኝ እንዲሁ ስሜን መጥራት ከከበዳችሁ እንደ አንድ ተራ ፋኖ ልትጠሩኝ ትችላላችሁ ይላል።
በአንድ ወቅት በአንድ የትግል አጋርነት ስብሰባ ላይ “በሕይወቴ ሰዎች ከጥፋታቸው ሳይቀጡ እንዲማሩ ነው የምፈልገው ግን አንድ ሰው ቅጣት ፍረድ ብባል እኔን ታላቁ ያለኝ ሰው እንዲቀጣ መፈለጌ አይቀርም” ብሏል።
*******************
አርበኛ እስክንድር ወደ ሚዲያ ተቀርፀው ያልወጡ የአማራ ፋኖን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ስልጠናዎች የሰጠባቸው ተከታታይ ስልጠናዎችም አሁን ለደረስንበት የትግል ምዕራፍ ከባድ አስተዋጽዖ አለው። በዚህ ሂደትም አንድ ህዝብ ነጻነቱን ለማግኘት የሚያስችለውን የህልውና ትግል ለመታገል መጀመሪያ በጠላት ያልተጠለፈ ወጥ ድርጅት መመሥረት ሲችል ነው የሚለው ነጥብ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ይህም እኔ በአቅራቢያ ከምታገልበት ሸዋ ግምባር የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ተመሠረተ ሲባል ጥይት ተኩሰው ብሥራቱን ያሰሙት የትግል ጓዶቻችን አንድ ድርጅት መመሥረት የማሸነፊያ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ያስጨበጣቸው እርሱ ነበር።
በትግል ሂደት ውስጥ በሠራዊት አመራር ላይ የእርስበርስ ግጭቶች ፣የሥነምግባር ግድፈቶችም ሲፈጠሩ ጉዳዩን ያልተረዱ አካላት እስክንድር ነጋ እንደፈፀመ ሲዘልፉት እና ሲያሙት እሱ ግን በጉዳዩ ላይ እውቅና ሳይኖረው እንኳን በትህትና ችግሮችን ሳይገፋ በፀጋ ይቀበል ነበር፡፡ ለማስረጃ ያህል ፤
ዶላር እንደበላ ፣አላማው ትግል ሳይሆን የስልጣን ፍላጎት እና ትግል ጠላፊነት ነው ብለው ዱሮ ከ11 ዓመት በላይ ጨለማ ቤት አስረው ላሰቃዩት ወሮ በላዎች እንደሚሰራ ዘሩም ከነሱው እንደተወለደ እና አማራ እንዳይደለ ሲሳለቁበት ይህን ሁሉ እውነት ጊዜ ይገልጠዋል በማለት በፈገግታ ነበር የሚያልፈው።
የአፋሕድ ሊቀመንበር ሳለ በአማራ ጠቅላይ ግዛት ፋኖ አመራሮች የስልጣን ፍላጎት ላይ እንዴት ነህ የሚል ጥያቄ ሲጠይቁት የምናስበው የአማራን ያልተጠለፈ ወጥ ድርጅት ማቆም ላይ እንጂ የግለሰብ የስልጣን ፍላጎት አሳሳቢ አለመሆኑን ድርጅት በመሰረትን ማግስት የሚሆነውን አብረን የምናየው ይሆናል ነበር ያለው። ይህ አነጋገሩ የምናምንባቸውን አመራሮች ካስቀመጥን ድርጅት ካቆምን እኔ ያኔ መሪዎችን እያገዝኩ ግባችንን ማሳካት ነው የሚል ሃሳብን ሰንዝሯል። የዚህ ታላቅ ሰው ቃል እውን መሆኑን የተረዳሁት በዚህ ሰሞን ያስገባውን ማመልከቻ ስመለከት ነው። እንደ ቅርበቴ መሪነቱን እንደማይፈልግ ሲያመለክትም በድርጅቱ መመሥረት በመሪዎችም መዋቀር ደስ እያለው እንጂ በመቀየም እና በስልጣን አነሰኝ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ።
ታላቁ እስክንድር ነጋን ታላቁ የሚያሰኘውም ስንቶች ለተራ ጉዳዮች ሳይቀር ሲዋሹ እና ሲያስመስሉ እሱ ግን ከአፉ ለምትወጣው እያንዳንዷ ቃላት እና ውሳኔ እጅግ የተጠነቀቀ ነበር። አርበኛው ሞት አይፈራም ፣ወሬ እና ዛቻ አሉባልታ እና መሠረተቢስ ዘለፋዎች ያስቁታል እንጂ ብዙም አያስደነግጡትም። ለማስረጃ ያህል ኮማንዶው ተሟርኳል ባህር ሃይሉ ተማርኳል በተባለበት የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ሠራዊት የጠላትን ጦር ሲገርፉት መጋቢት 7/2016 ዓ.ም አካባቢ የጠላት ከፍተኛ ትንቅንቅ ሲደረግ ከፍተኛ የድሮን አሰሳ ሲደረግ እናንተ ልጆች ናችሁ ለዚህ ለተገፋ ህዝብ ታስፈልጋላችሁ ራሳችሁን ተከላክላችሁ ውጡ እኔ የምችለውን ለህዝብ ለመስራት ሞክሬያለሁ አለን እንጂ ራሴን ላድን አላለም። በዚህ ዕለት በነበረ የጠላት ከፍተኛ ትንቅንቅ ምስክሬ አርበኛና ጋዜጠኛ ጌጥየ ያለው አብሮን ነበር።
**************
አርበኛው እውነት ነው፣ለህዝብ እና ለሃገር ጠቃሚ ነው ብሎ ለአመነበት ነገር ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ነው አይነቀነቅም። በዚህ ባህሪው በዚህ ልክ ያሳደጉትን ቤተሰቦቹን በጣም አደንቃለሁ። ከሱ ጋር ለመሟገት እና ለማሸነፍ በቂ ማስረጃ ይዞ መቅረብ እንጂ ማስረጃ እስካለው ልጅ አዋቂ ሳይል ሳይመርጥ ይወያያል።
አሁን ጠላት የፖለቲካ ጠለፋ ለማድረግ የሚጋጋጥበትን የድርድር ጉዳይ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የአፋሕድ አመራሮችን ለማወያየት ፍቃድ ሲጠይቁ በነበረን የጋራ የአመራር ስብሰባ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አይነት የፖለቲካ ጠለፋ ሊሞክሩ እንደሚችሉ ቀድሞ የነቃ ብልህ ሰው ነበር። በወቅቱም ውይይቱ እነዚህን እንግዶች አንወያይም ብንል ሃሳብ የምንገፋ ሽብርተኞች ከምንባል በውውይይቱ ሃሳባቸውን አዳምጠን ከአቢይ ጋር ተደራደሩ ካሉን ግን በምንም አይነት መንገድ አማራን ከጨፈጨፈ መንግስት ጋር አንደራደርም እንዳዉም በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ጥያቄ እናነሳለን ነበር ያለው። በወቅቱም በተሰጠ ብርቱ አቋም ድጋሚ እንዳይደውሉ ሊሆን ችሏል። ይህን ሃሳብ በውይይቱ ይህን የፖለቲካ ሴራ ማንሻፈፍ ሊሰራም እንደሚችል መላምቱን አስቀምጦ ነበር።
በነዚህ የውይይት አጋጣሚዎች የድርጅቱ አመራሮች አሁን ከድተው ከመንግሥት የገቡትንም ወደ ጠላት የመሄድ አዝማሚያቸውን በደንብ በመተንበይ ከፍተኛ የዕገዳ ውሳኔ ቢያሳልፍም በድምጽ ስለተበለጠ እንዲቀጥሉ ተደርጎ ነበር።
አርበኛው በንስር አይኖች ነገሮችን ይመለከታል በእምነቱም ጠንካራ ነው፡ የሌሎች እምነቶችንም በጣም ያከብራል ያሳለፋቸው የትግል ዘመኖችም ከፍተኛ ልምድ እንደሰጡትም ያስታውቃል። ብዙ ስሙን ስለሚያጠፉት ሰዎችም ምንም አይቀየምም በተሳሳቱት ነገር ላይ ብዙም አስተያየት አይሰጥም። በፋኖነት ውስጥ ምቾትን መፀየፍ አለብን የሚል መርህ አለው። በትግሉ ውስጥ ቅንጡ አለባበሶች ፣አመጋገቦችን ፣አልኮል መጠጣት እና ሥጋ መብላትን ዋናውን አላማ ያስረሳሉ የሚል አስተምህሮ ቢኖረውም እኛ ግን ብዙም አልተረዳነውም ነበር። በትግሉ ሂደት ውስጥ ምግብ ህዝብ ይችለናል በየትኛውም መንገድ የሚገኘው ገንዘብ ለተተኳሽ እና ለመድሃኒት ብቻ መዋል አለበት ብሎ ስለሚያስብ በአጠገቡ ለማንኛውም ታጋይ የገንዘብ አበል እና ቅንጡነትን አይፈቅድም ይህ ደግሞ ባልገባቸው ሰዎች ዘንድ ቅሬታ ያስነሳበት ነበር።
የስልጣን ተቀናቃኞች ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ አካላት ከሚሰነዝሩት ትችት ቤቱን ጥሎ የዘመተ ታጋይ በፈለገው እይታ ሊተቸን መቻሉ በጣም ትክክል ነው ከምቾታቸው ሳይወርዱ ከጨፍጫፊው መንግስት ሳይርቁ የሚተቹን ግን ትክክል አይደሉም ይላል።
************************
የስብእና ገደላ ለማድረግ የሚዲያ ዘመቻ የተደረገውን ሁሉ ስመለከት እኔም እንደ አንድ ተራ ታጋይ ጀነራል አሳምነው ጽጌም በህይወት ኖሮ ቢሆን ይሄው ያልተመዘነ የወሬ ስላቅ ሊደርስበት እንደሚችል እገምታለሁ።እርግጥ ይህ ዓለም ክርስቶስ ይሰቀል ሽፍታው ግን ይውረድ ያለ መሆኑን አስበዋለሁ። ከትላንት የኢትዮጵያ ታሪክም ብዙ ታጋዮች እና ምሁራኖቻችንን ለህዝብ ስንት መከራ ሲከፍሉ ጉንጭ ከመምጠጥ የዘለለ ነገር አልተደረገላቸውም። በስማቸው መንገድ እንኳን አልተሰየመላቸውም የታጋይ ወሮታው ወርቅ ላበደረ ጠጠር ፣እህል ላበደረ አፈር ነው። መጽሐፍም ነቢይ በገዛ አገሩ አይከብርም በተለይ ደግሞ በዘመዶቹ ዘንድ እንዳለው እኛ መሳለቂያ ያደረግነው ታላቁ እስክንድር ነጋ በአሜሪካ መንግስት መሪዎች እና ህዝቦች ዘንድ ታላቅ ክብር እና ዝና እንዳለው ለማወቅ ዊክፒዲያ ገጽ ላይ ስሙን መጻፍ በቂ ነው።
************************
ክቡራን አንባቢዎቼ ይህን ጽሑፍም ስጽፍ እውነት ባለመስከሬ እንዳልፀፀት እንጂ ታላቁ እስክንድር ተገፍቷል ብየ ለመጮህ አይደለም ይህንንም እንዲመሰክርለት ፍቃዱን አልጠየቅሁትም ብጠይቀውም አይፈቅድልኝም፣እንዲሁ የግል መብቴን ተጠቅሜ ጻፍኩት እንጂ።
አርበኛ እስክንድር ነጋ ስለትግል ፍታውራሪያችን ስለ ዘመነ ካሴም ጀግንነት ይናገራል ስለማንኛውም ሰው ደካማ ጎን አያወራም ሰዎች ስለ እስክንድር ነጋ ገምተው የሚጽፉት ማጠልሸት ግን ከእውነታው ሰአማይ ከምድር የሚርቀውን ያህል የራቀ ነው።
ይህ አርበኛ አሁን በስኬት ባቆምነው “አፋብን” መሪ ድርጅታችን በእውቀት በትግል በማንኛውም በሱ ዘንድ ባለ ነገር ሁሉ በጸሎት ሳይቀር ከዳር ለማድረስ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እንደሚከፍል አልጠራጠርም።
*************************
የግል አስተያየት ስለ ታላቁ እስክንድር
በአርበኝነት ከምኑም እንደማልደርስ አውቃለሁ ግን ደግሞ ሰዎች ያሙትን ሁሉ መጥፎ ነገር ሳይሆን በመገኘቱ ለእርሱ በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት ነው ። ታላቁን በስልጣን ፣በገንዘብ ፣በጥቅም ማማት ድመትን በቆሎ መጠርጠር ነው። ለእርሱ ይህ ድርጅት መመሥረቱ እርሱም በቅንነት ከዚህ የትግል ላይ ትግል ነጻ የአማራ ፋኖ ታጋይ መሆኑ በትግል ውስጥ የተገኘ የግሉ ድል ነው። ሃሜተኞችን እና ተሳዳቢዎችን እንደ ክርስቶስ በፍቅር እና ትህትና አሸንፏቸዋል። ይህ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቹ ፣ለወዳጆቹ ታላቅ ደስታ ለጠላቶቹ መልካም ትምህርት ነው ብየ አስባለሁ። በዚህም አጋጣሚ ታላቁ እስክንድር ነጋ ከትግሉ እንደተገፋ ሳይሆን ልንቆጥረው የሚገባው የንጽሕና ካባን እንደተቀዳጀ እልፍ ገዳይ አርበኛ በንጽሕናው እንዳሸበረቀ ለድርጅት መሪዎቻችን ደጀን እንደሆነ እቆጥረዋለሁ።
በቋንቋ ግድፈቶች ያበላሸሁትን ንባብ አቃንታችሁ በማንበብ እና በመረዳት በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ምንጭ፦ አርበኛ መምህር ይብዛወርቅ መስፍን (ዮቶር)።



Comments